ቅ/ሲኖዶስ: በፀረ ተሐድሶ ኑፋቄ አጀንዳ መወያየት ጀመረ፤ ሕዋሱ ምልምሎቹን በኤጲስ ቆጶስነት ለማሾም እየሠራ እንዳለ ተጠቁሟል

  • የተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ጥቆማና ምርጫ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ተጠይቋል
  • ብፁዓን አባቶች፣ በአደረጃጀትና በእንቅስቃሴ የአህጉረ ስብከታቸውን ተሞክሮ አቀረቡ
  • የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ የወራት አፈጻጸም በጥቅሉ ተገምግሟል
  • በልዩ ጽ/ቤቱና በአባ ቃለ ጽድቅ ያለው የኑፋቄው ስጋት ዛሬም ትኩረት ተሰጥቶታል
  • የፀረ ተሐድሶ ጉባኤውን ከአጥቢያ እስከ አህጉረ ስብከት ማዋቀሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል
  • ኑፋቄውን በሚያጋልጡና በሚያመክኑ ተጨማሪ ስልቶች ላይ ምክክሩ ነገም ይቀጥላል

*                     *                     *

Holy synod Gin2008

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ፤ አገልግሎቷም የተሟላ እንዲኾን የማድረግ ዓላማዎች ያሉት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለትምህርተ ሃይማኖታችንና ለመዋቅራዊ አንድነታችን የህልውና ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ለማጋለጥና ለማምከን ስለሚደረገው የመከላከል እንቅስቃሴ መወያየት ጀመረ፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ በዛሬ፣ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው፣ “ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አንፃር የመናፍቃን እንቅስቃሴ ጉዳይ” በሚል በተ.ቁ(15) በያዘው አጀንዳ መነጋገር እንደጀመረ ተገልጿል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ከኑፋቄው ተጽዕኖና ተጨባጭ አደጋዎቹ በትይዩ፣ በማስረጃ ለማጋለጥ እና በትምህርት ለመከላከል ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎችና የወሰዷቸውን ርምጃዎች፣ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተሞክሮ በመነሣት አብራርተዋል፡፡

በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ በተወሰነው መሠረት፣ ማኅበረ ካህናትን፣ ማኅበረ ምእመናንን፣ የሰንበት ት/ቤቶችንና ማኅበረ ቅዱሳንን ያሳተፈየፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ በወረዳዎችና በአጥቢያዎች በማቋቋም የሚካሔደው አድማሳዊ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ ተጠናክሮ እንደቀጠለ፣ ከብፁዓን አባቶች ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምዕራብ ሸዋ፣ ጅማ እና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት በአርኣያነት የተጠቀሱ ሲኾን፣ ሌሎች አህጉረ ስብከትም በአርኣያነት እንዲማሩበ በውይይቱ አጽንዖት ተሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ የወራት እንቅስቃሴ በጥቅሉ የገመገመ ሲኾን፤ በየአህጉረ ስብከቱ የሚቋቋሙት የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤዎች ዕቅዶቻቸውንና አፈጻጸሞቻቸውን እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ በኢንፎርሜሽንና በሪፖርት እንዲያቀርቡና ከማዕከል በሚሰጠው አቅጣጫና መመሪያ መሠረት እንዲያገለግሉ ቀደም ሲል የተላለፈው ውሳኔ ተጠብቆ ሊሠራበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

Holy Synod01
የብፁዓን አባቶች ገለጻ እንደሚያሳየው፣ በየአህጉረ ስብከቱ የሚደረገው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ የሚያበረታታ ቢኾንም፣ ኑፋቄው በቤተ ክርስቲያናችን ማንነትና ማዕከላዊ አንድነት ላይ ከጋረጠው አደጋ አኳያ ገና አጥጋቢ/በቂ እንዳልኾነ በምልዓተ ጉባኤው ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ለዚኽም በቃልም በኅትመትም በየጊዜው ለሚረጩት ኑፋቄዎች በቂ ጽሑፋዊ ምላሽ በመስጠት ረገድ ያሉ ውስንነቶች በዓይነተኛ ማሳያነት ተጠቅሰዋል፡፡

ከአህጉረ ስብከቱ ባሻገር በማእከል፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ጉዳይ መምሪያው እንደ አደረጃጀት ማሻሻያው ኹሉ ከኑፋቄው ሤራም አንፃር በጥልቀት እንዲፈተሽ ምልዓተ ጉባኤው ሲያሳስብ፣ መነሻው፣ የመምሪያው ዋና ሓላፊ መልአከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ የእምነት አቋም ነበር፡፡ በትእዛዛቸው በሓላፊነት ላይ ያስቀመጡት ርእሰ መንበሩ፣ ስለ ግለሰቡ ማስረጃ ከቀረበላቸው ርምጃ እንደሚወስዱ ዛሬም በምልዓተ ጉባኤው ፊት አረጋግጠዋል፡፡

የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄው ወኪሎች ሌት ተቀን እየሠሩበት ያለው ሌላዊ ወቅታዊ ጉዳይ ደግሞ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአጀንዳነት የያዘውየአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የኑፋቄው ሕዋስ፣ በሢመቱ አጋጣሚ ምልምሎቹን አስርጎ በማስገባት በማዕርገ ክህነቱ ከፍተኛ ቦታ ለመያዝ እየሠራ በመኾኑ፤ በዕጩነት በሚቀርቡ ቆሞሳትና መነኰሳት ጥቆማና በምርጫው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡ የኑፋቄው የውስጥ አርበኞች፣ “የራሳችንን ሰው ለማስገባት ሠርተናል፤ ዝግጅታችንን ጨርሰናል”ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡

በዚኽ ረገድ የሚፈጠር መዘናጋት፣ የኑፋቄው ሕዋስ፣ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት የደረሱ ኹለት ሦስት ኤጲስ ቆጶሳትን ብቻ ይዞ የቤተ ክርስቲያንን ማእከላዊ አስተዳደር ለመፈታተንና ከተሳካለትም ለማናጋት በመሣርያነት የሚጠቀምበት በመኾኑ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በተለይ የተሿሚዎችን ጥቆማ በቀኖናውና በሕጉ መሠረት፣ ከአህጉረ ስብከት ጀምሮ የማኅበረ ካህናትን፣ የማኅበረ ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ፤ ከሲሞናዊነትና ከጎጣዊ መሳሳብ በመጠበቅ አደጋውን ለመቀነስ እንደሚቻል ተገልጧል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ውጤታማና ዘላቂ በኾነ መልኩ ለማጋለጥና ለመከላከል ያስችላሉ ባላቸው ተጨማሪ ስልቶች በነገው የግማሽ ቀን ውሎው በመምከር፣ ተጋድሎውን የሚያጠናክርና በመመሪያነት የሚያገለግል ዐቢይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

haratewahdo

Advertisements

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s