በካይሮ መንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል የቦምብ ጥቃት: ከ25 በላይ ምእመናን ተገደሉ

በካይሮ መንበረ ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል የቦምብ ጥቃት: ከ25 በላይ ምእመናን ተገደሉ

ፕሬዝዳንት ኤል – ሲሲ፣ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ዐውጀዋል
ፖፕ አቡነ ታዎድሮስ የግሪክ ጉብኝታቸውን አሳጥረው ተመልሰዋል
በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን ጸሎተ ፍትሐት ይመራሉ

* * *
በግብጽ – ካይሮ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ዛሬ ረፋድ ላይ የነጐደ ቦምብ፣ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ ከነበሩት ምእመናን ቢያንስ 25ቱን ገድሎ ከ49 ያላነሱትን ማቁሰሉን የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው፣ የኮፕት ኦርቶዶክስ መንበረ ፓትርያርክ ከኾነው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ጋር ኩታ ገጠም ኾኖ በአንድ ቅጽር በሚገኘው በዚኹ ቤተ ክርስቲያን የሴቶች ምእመናን በሚቆሙበት አንቀጽ እንደኾነ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃል አቀባይ ቀሲስ ፖል ሐሊም ተናግረዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኑ የኋላ መቀመጫ በሴት ቦርሳ ውስጥ እንዳለ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ የፈነዳው ቲ.ኤን.ቲ ቦምብ፣ 12 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን ተጠቅሷል፡፡ ምእመናኑ በእሑድ ሰንበት ጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንደነበሩና ቁስለኞች ወደተለያዩ የከተማይቱ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን የአገሪቱ የጸጥታ አካላት አመልክተዋል፡፡

በአገሪቱ የብዙኃን መገናኛዎች እየተላለፉ ያሉ የቪዲዮ ምስሎች፣ በአደጋው የወደሙና የተሰባበሩ መስኮቶች፣ ወንበሮችና የጣሪያው ውስጠኛ አካል፤ በደም ከተለወሱት የሟቾችና የተጎጅዎች አልባሳት ጋር በቤተ ክርስቲያኑ ወለል ላይ እንደተበታተኑና እንደተመሰቃቀሉ ያሳያሉ፡፡

ከአንገቷ በላይ ያለው አካሏ የተቆረጠ አንዲት ሴት ከቦታው ስትገለል መመልከቷን ለአሶሽየትድ ፕረስ የዜና ወኪል የተናገረች የዓይን እማኝ፤ የሚበዙት የጥቃቱ ሰለባዎች ሕፃናትና ሴቶች እንደኾኑ ተናግራለች፤ “ሕፃናት ልጆችም ነበሩ፤ ምን በበደሉ ይኼ ይደረግባቸዋል፤ ይኼን ዓይነቱን ጭካኔ ከማይ ምነው ሞቴን ከእነርሱ ጋር ባደረገው!” ስትልም የኹኔታውን አሠቃቂነት ትገልጻለች፡፡

በጥቃቱ የተመረሩ የኮፕት ክርስቲያኖችና ሙስሊም ወገኖች፣ ቀትር ላይ በካቴድራሉ በመሰብሰብ ቁጣቸውንና ተቃውሟቸውን በአንድነት አሰምተዋል፤ የአባስያ ጎዳናን ጨምሮ ወደ ካቴድራሉ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ በጸጥታ ኃይሎች ታግረው አካባቢው ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገበት እንዳለም ተዘግቧል፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመው የዛሬው ጥቃት፤ እ.አ.አ በ2013፣ በካቴድራሉ አቅራቢያ በሐዘን ላይ ከነበሩ ምእመናን ኹለቱ ከተገደሉበት ፍንዳታ በኋላ የደረሰና በዚኹ ሳምንት በተለያዩ የከተማይቱ ቦታዎች ከታዩት መሰል ተከታታይ አደጋዎች ሦስተኛው ነው፡፡

የቦምብ ጥቃቱን የኰነኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታሕ ኤል-ሲሲ፣ ሰለባዎቹ የሚታሰቡበት የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ዐውጀዋል፤ የአደጋው ጠንሳሾች፣ አድራሾችና ተባባሪዎች የእጃቸውን እንደሚያገኙ መናገራቸውንም የአገሪቱ ቴሌቭዥን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ የኮፕት ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች የአሠቃቂ ሽብር ዒላማ በመኾን ላይ እንዳሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸው፤ ግብጽ፣ ከኹኔታው አንድነቷን አጽንታና የበለጠ ተጠናክራ ትወጣለች፤ ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ማርቆስ ሐዋርያዊ የአሌክሳንደርያ ፖፕና የመላው አፍሪቃ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ፣ በግሪክ በማካሔድ ላይ የነበሩትን ጉብኝት በማሳጠር ወደ ካይሮ በመመለስ ላይ እንዳሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምንጮች ጠቅሶ የዘገበው አኽራም ኦንላይን፤ እንደ ደረሱ በቀጥታ ጥቃቱ ወደተፈጸመበት ስፍራ ያመራሉ፤ ብሏል፡፡

ዘግይተው ከመንበረ ፖፑ የወጡ መረጃዎች፤ በጥቃቱ የተገደሉት ክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ነገ ሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 ቀን፣ በካይሮዋ ናስር ከተማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸምና ሥርዓቱም በፖፕ አቡነ ታዎድሮስ እንደሚመራ ይጠቁማሉ፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እ.አ.አ በ2013 ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ግብጽ በጽንፈኛ እስላማዊ ሚሊሻዎች የሽብር ጥቃት እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ጽንፈኞቹ፣ ክርስቲያኖችን፡- በሙርሲ መወገድ ተባብራችኋል፤ በሚል ይወነጅሏቸዋል፡፡

ለዛሬው ጥቃት እስከ አኹን ሓላፊነቱን በይፋ የወሰደ አካል ባይኖርም፣ ከአጠቃላዩ ሕዝብ 10 በመቶ(ከ10 እስከ 14 ሚሊዮን) ያኽል የሚኾኑት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች፣ በሰበብ አስባቡ ከሚፈጸምባቸው ሥርዓታዊ መድልዎ ባሻገር ያሉበትን ሠቆቃ የሚያሳይ ነው፤ ተብሏል፡፡

No automatic alt text available.
Image may contain: one or more people and people standing
Image may contain: 1 person, standing, crowd, sky and outdoor
Image may contain: 1 person, beard
Advertisements

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s