ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በጋራ ለመደራደር ያደረጉት የመጀመሪያ ጥረት አልተሳካም

ሃያ አንድ አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በተናጠል ወይም በጋራ ለመደራደር ለመወሰን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ያደረጉት ስብሰባ ባለመሳካቱ፣ በተናጠል ውይይት የሚያደርጉት ዕድል እየሰፋ መምጣቱ ተጠቆመ፡፡

ዋናው ድርድር ከመጀመሩ በፊት ድርድሩ የሚመራባቸው ዝርዝር የሥነ ሥርዓት ደንብ ላይ ውይይት እያካሄዱ ያሉት 21 አገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ አምስት ዙር ውይይት አድርገዋል፡፡ በመጪው መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚካሄደው ስድስተኛ ዙር ውይይት በደንቡ ላይ የሚደረገው ውይይት እንዲጠናቀቅ ባለፈው ሳምንት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን ለመቋጨት ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተናጠል አልያም በቡድን ወይም በተወካይ አማካይነት መደራደር እንደሚፈልጉ ራሳቸው እንዲወስኑ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት፣ 21 ፓርቲዎች መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ተገናኝተው ለመወሰን ተቀጣጥረው ነበር፡፡ ነገር ግን በዕለቱ የ12 ፓርቲዎች ተወካዮች ብቻ ናቸው የተገኙት፡፡

ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይ በተናጠል ወይም በቡድን ወይም በተወካዮች ለመደራደር እንዲወስኑ ሐሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በቡድን ሲደራደሩ የሚቀር የተለየ አጀንዳ ካለው አካል ጋር የተናጠል ድርድር ለማድረግም ፈቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡ በዕለቱ የተገኙት ፓርቲዎች በአንድ ተወካይ ለመቅረብ ያላቸው ሐሳብ በዚሁ ስምምነት የተነሳ እንደተደናቀፈ ተገልጿል፡፡ ከተገኙት ፓርቲዎች መካከል ኢዴፓ፣ ሰማያዊና ኢራፓ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዕለቱ ካልተገኙ ፓርቲዎች መካከል መድረክ፣ መኢአድና ወለኔ ተካተዋል፡፡ ወለኔ የማንነት ጥያቄ የማያራምድ በመሆኑ በተወካይ ለመደራደር እንደማይችል መግለጹ ታውቋል፡፡

የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፣ በመርህ ደረጃ ጠበብ ብሎ በተወካይ አማካይነት መደራደርን ኢዴፓ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡ 22 ፓርቲዎች ባደረጉት ስምምነት መሠረት በዕለቱ የተገኙት ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የሐሳብ ልውውጥ ቢያደርጉም፣ በአንድ ተወካይ ቡድን መደራደርን ተግባራዊ እንዳላደረጉም አክለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ፓርቲዎቹ በተናጠል ከኢሕአዴግ ጋር የመደራደር ዕድላቸው እየሰፋ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን አሁንም ጠበብ ብለን በተወካዮች አማካይነት ለመደራደር ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡

መድረክ በአምስኛው ዙር ውይይት ከኢሕአዴግ ጋር ለብቻው ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህ የተነሳ በሰኞው ስብሰባ አለመገኘቱ ብዙም የሚገርም አልሆነም ተብሏል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተናጠል ከሚደራደሩ ይልቅ በጋራ ቢደራደሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ያሳስባሉ፡፡ ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ‹‹ኢሕአዴጎች በባህሪያቸው ትምክህተኞች ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር የሚቻለው ሲፈቅዱና ፍላጎት ሲኖራቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በቡድን ወይም በተወካይ መቅረብም ሆነ በተናጠል መደራደር ብዙ ልዩነት ያለው አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና መድረክ በተናጠል የመደራደር ሐሳብ ለማቅረብ የተገደደው በጋራ ለመሥራት የመረጣቸው የሰማያዊና የመኢአድ ፓርቲዎች የፀና አቋም ስለሌላቸው  እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

‹‹መድረክ በአቋሙና የፖለቲካ ምኅዳሩ እየፈጠረ ካለው ችግር አኳያ ለሰማያዊና ለመኢአድ ይቀርባል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲህ ዓይነት ጫና ደረሰብን ሲሉ አላይም፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ጊዜ ወስደን ተነጋግረን ነበር፡፡ በኋላ ሐሳባቸውን ቀይረው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመሆን መረጡ፤›› ብለዋል፡፡

ከየካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ ፕሬዚዳንት መሆናቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፀደቀላቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ ግን፣ የጋራ አጀንዳ እስካለ ድረስ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ቢሆን አብሮ ለመሥራት ሰማያዊ ዝግጁ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የጋራ አጀንዳዎቻችን አንድ እያደረጉን ይመጣሉ የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በሰኞው ስብሰባ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱ መነገሩ ትክክል እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት አምስት ዙር ውይይቶች በተቃራኒ የሰኞው ስብሰባ የተቀናጀና ኃላፊነት ወስዶ የሚያስተባብር አካል ያልነበረው ነው፡፡ የተሻለ ቅንጅትና የማስተባበር ሥራ ቢሠራ የተለየ ለውጥ ሊኖር ይችላል፤›› ሲሉም አቶ የሺዋስ አክለዋል፡፡

ኢሕአዴግን በመወከል በፓርቲዎች ድርድር እየተሳተፉ የሚገኙትና የውይይቱ ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በቡድን በቡድን ከኢሕአዴግ ጋር እንደራደር የሚል ጥያቄ ለገዢው ፓርቲ እንዳልቀረበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ድርድሩ በጋራ ይሁን በተናጠል የሚወሰነው በሚቀርበው አጀንዳ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ ኢሕአዴግ ለተመሳሳይ አጀንዳ የተለያየ ድርድር አያደርግም፡፡ የተለየ አጀንዳ አለኝ ከሚል ማንኛውም ፓርቲ ጋር ለመደራደር ግን ዝግጁ ነን፡፡ ምርጫው ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተተወ ነው፤›› ብለዋል፡፡

Advertisements

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s