ሰበር ዜና – የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፥ መናፍቁን አሰግድ ሣህሉን አውግዞ ለየ!

 

ለኑፋቄ ትምህርቱ እና ሥራዎቹ ምላሽ እንዲሰጥባቸው አዘዘ
በቤተ ክርስቲያን ስም በፈጸማቸው አድራጎት በሕግ ይጠየቃል
በአጭበረበረው 6 ሚሊዮን የዐሥራት ብር፣ እየተመረመረ ነው
ለሙዝየም የተለገሰውን “ወንጌል አስፋፋበታለሁ” ብሎ ክዷል
ከ37 ያላነሱ ማኅበራትና ግለሰቦች ከማበር እንዲቆጠቡ ተወሰነImage may contain: 1 person

* * *
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬ፣ ግንቦት 3፣ ኹለተኛ ቀን የቀትር በኋላ ውሎው፣ ኑፋቄን በኅቡእና በገሃድ በማስፋፋት፣ ምእመናንን በማጠራጠርና በማስኮብለል፤ በተለያዩ ስልቶች የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እየሰበሰበ ለቅሠጣና ለግል ጥቅሙ በማዋል የሚታወቀውን አሰግድ ሣህሉን በማውገዝ፣ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለየ፡፡

ምልአተ ጉባኤው ውግዘቱን ያስተላለፈው፣ ራሱን ‘ቃለ ዓዋዲ’ እያለ የሚጠራውና በአሰግድ ሣህሉ የሚመራው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቡድን፣ በቤተ ክርስቲያን ስም በመንቀሳቀስ እየፈጸመ ስለሚገኘው የኑፋቄና የወንጀል ተግባራት፤ በቪድዮ እና በሰነድ ተደግፎ የቀረበለትን ማብራሪያ ከመረመረ በኋላ ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤት አባልና አመራር ከነበረበት ወቅት ጀምሮ በተጠረጠረበት የሃይማኖት ሕጸጽ፥ ምክር፣ አመክሮና ቀኖና በተለያዩ ጊዜአት ሲሰጠው እንደነበር የጠቀሰው ማብራሪያው፤ ይኹንና አሰግድ፣ ምክሩንና ተማጥኖውን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበረና በቀኖናውም ከስሕተቱ ሊታረም እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

ስውር የቅሠጣ ተልእኮውን ለማራመድ በማሰብ፣ ያለሰበካው በተመዘገበበት የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ የሰንበት ት/ቤት፣ በ1985 ዓ.ም. በአባልነት ተመዝግቦ በአጭር ጊዜ፥ ‹‹የትምህርተ ሃይማኖት አስተማሪ››፣ የሥራ አመራር አባልና የትምህርት ክፍል ሰብሳቢ ለመኾን ቢበቃም፤ ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያን ጉያ በማውጣት የሚታወቁትንና በኋላም ኑፋቄአቸው በማስረጃ ተረጋግጦ ተወግዘው የተባረሩ ግለሰቦችን ወደ ሰንበት ት/ቤቱ እየጋበዘ እንዲያስተምሩ ያደርግ እንደነበር ተወስቷል፡፡

በተለይ፣ “ሙሉ ወንጌል” እየተባለ የሚጠራውን የፕሮቴስታንታዊ ድርጅት አዳራሽ በማዘውተር፤ አንዳንድ ወጣቶችንም ለመውሰድ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ፣ በሰንበት ት/ቤቱ የሥራ አመራር ጥብቅ ክትትል በማስረጃ ተጋልጦና ተመስክሮበት ከሰንበት ት/ቤቱ እንደታገደ በማብራሪያው ተገልጧል፡፡

የተሐድሶ ኑፋቄ በስውር ይራመድባቸው በነበሩ የቤት ለቤት የጽዋ ማኅበራትና በየአዳራሹ በሚካሔዱ ጉባኤያት፣ የሰንበት ተማሪዎችን እያግባባ እንደሚወስድ፤ ‹‹ቅዱስ ቁርባን አያድንም››፤ ‹‹የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ተቀበልንም አልተቀበልንም ለውጥ የለውም›› በማለት እንደሚያጠራጥር፣ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አኹንም በአብ ቀኝ ቆሞ ያማልዳል›› በማለት በይፋ እንደሚከራከር፤ ክብረ ቅዱሳንንና ክብረ ክህነትን ንቆ ሲያበቃ ሌሎችም እንዲንቁ እንደሚቀሰቅስ የሰንበት ት/ቤቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማታው መርሐ ግብር፣ በ1993 ዓ.ም. የተመዘበው አሰግድ፣ በክፍል ውስጥ በጥራዝ ነጠቅነት በሚቀሰቅሳቸው በኑፋቄ የታጀሉ ንትርኮች ተጠርጥሮ፣ በተቋቋመ የደቀ መዛሙርት ኮሚቴ አማካይነት በቀረበው ሪፖርት፣ ዲፕሎማው ታግዶበት እንደነበርና ቆይቶም እንደተመለሰለት ተገልጿል፡፡

በ2003 ዓ.ም.፣ በዲግሪው መርሐ ግብር ትምህርቱን ቢቀጥልም፣ ለመንፈሳዊ ኮሌጁ ያቀረበውና ለቅበላው፣ እንደ መስፈርት መሟላት የነበረበት የሰበካ ጉባኤ አባልነት ማስረጃ፣ የደብር ሓላፊዎችን በማጭበርበርና በገንዘብ በመደለል የተገኘ እንደኾነ በመረጋገጡ፣ በኮሌጁ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንደታገደና ኮሌጁም እንዳላስመረቀው ተጠቅሷል፡፡

አሰግድም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ መንፈሳዊ ኮሌጁን ቢከሥም፣ ኮሌጁ፥ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ለማስፋፋትና አማኞቿን ለማስተማ ያቋቋመችው ስለኾነ በዚህ ጉዳይ ፍ/ቤት ውሳኔ ለመስጠት አይችልም፡፡ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን አለው ከተባለ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደ መግባት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ስለሌለው መዝገቡን ይዝጋልኝ፤” በማለት ሲከራከር ቆይቶ፣ ታላቅ ድል ኾኖ ሊመዘገብና አብነታዊ ኾኖ ሊወሰድ የሚችል ውሳኔ ከፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አግኝቷል፡፡

ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት፣ በመዝገብ ቁጥር ሰ/መ/ቁ 77479 በቀን 06/02/2005 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፥ አሰግድ ሣህሉ ክሥ ያቀረበበት ጉዳይ፣ “በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 እንደተደነገገው፣ በፌዴራል ፍ/ቤቶች አማካይነት በፍርድ ሊያልቅ የሚገባው ጉዳይ (justiceable) አይደለም፤” በማለት በይኗል፡፡ በዚኽም መሠረት የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት፣ ሐምሌ 7 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠው ብይንና ፍርድ፣ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ ኅዳር 28 ቀን 2004 ዓ.ም የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ፥ “የፍርድ ጉድለት የለበትም” በሚል ያሳለፈውና የመጨረሻ ዳኝነት የኾነው ትእዛዝ እንደተሻሩ አስታውቋል፡፡ (LINK) መንፈሳዊ ኮሌጁም፣ ተቋማዊ ሥልጣኑን መሠረት በማድረግ፣ መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ በተጭበረበረ ማስረጃ ያገኘውን ዲግሪ በማገድ ጥቅም አልባ እንዳደረገው በማብራሪያው ተመልክቷል፡፡

ከዚኽ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን በይፋ ወጥቶ፣ በየአዳራሹ በገሃድ በመሰብሰብ እንዲኹም፣ በተለያዩ ከተሞች የሥልጠና ቦታዎችን እያመቻቸና ኅቡእ ቡድኖችን እያደራጀ ቅሠጣውን እንደቀጠለ ለምልአተ ጉባኤው ተገልጿል፡፡ በማሠልጠኛነት የሚጠቀምበትና “የመዳን ትምህርት” በሚል የተዘጋጀ አንድ ጥራዝም ለምልአተ ጉባኤው እይታ ቀርቧል፡፡

ያለቤተ ክርስቲያን ዕውቅና፣ ‘ቃለ ዐዋዲ’ በሚል በኢቢኤስ የሳተላይት ቴሌቭዥን፣ በ2005 ዓ.ም. በጀመረው ፕሮግራሙ፣ “ወልድ ፍጡር” ብሎ አርዮሳዊ ክሕደት እስከ መናገር [በዚኽ ምድር ላይ፣ ሞቼ ነበር፤ ተነሣኹ፤ ብሎ ሲናገር የሰማነው፣ ሲያወራ ያየነው አንድም ፍጡር የለም፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር] መድረሱ በማብራሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ በተለያዩ ጊዜያት በፕሮግራሙ ያሠራጫቸው ግልጽ ኑፋቄዎች፣ በይዘታቸው ተለይተው ምልአተ ጉባኤው እንዲመለከታቸው ተደርጓል፡፡

የኢቢኤስ ፕሮግራሙ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሲዘጋም፣ በ“ቃለ ዐዋዲ መርሐ ግብር” ቀጥሎ፣ በተለይ በቦሌ የሸማቾች ኅብረት አዳራሽ በየወሩ፣ ከፍተኛ ኪራይ በሚከፍልበት ግቢም በሳምንት ኹለት ቀን፦ “የፈውስና የትምህርት መርሐ ግብር” በሚል እንዲኹም፣ “ቃለ ዓዋዲ ቲቪ ፕሮግራም” በተባለው የፌስቡክ ገጽ፣ ኑፋቄውን እያስፋፋ እንደሚገኝ ቀርቧል፡፡ የፈውስ አገልግሎት፤ በሚለው ፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ፣ “በልጅነታችን እንደምንጫወትበት፣ ሰይጣንን እንደ ቅጠል ኳስ ጢባጢቤ ነው የምጫወትበት፤” ይላል፣ አሰግድii

በኅቡእ ከተሰበሰቡት ማስረጃዎች ይልቅ በገሃድ የሰበካቸውና ኑፋቄውን በተጨባጭ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በርከት ብለው የተካተቱበት ማብራሪያ፣ ለ45 ደቂቃዎች ያኽል ከተሰማ በኋላ፣ ርእሰ መንበሩን ጨምሮ የምልአተ ጉባኤው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሡ ሲኾን፣ ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በኑፋቄ እንቅስቃሴዎቹ፣ ከአሰግድ ሣህሉ ጋራ መታየት ያለባቸው ተባባሪዎቹ ይኖሩ እንደኾን ለቀረበው ጥያቄ፣ 37 ማኅበራትና ግለሰቦች በአበርነት መለየታቸው ተጠቅሷል፡፡

“ቃለ ዐዋዲ” ከሚለው መጠሪያ ጀምሮ፣ በሕግ ሊታዩ ስለሚገባቸው ጉዳዮችም በተነሣው ሐሳብ፣ አሰግድ ሣህሉ፥ የክህነቱን ሥልጣን በያዙ መሰሎቹና በራሱም የተለያዩ የማጭበርበሪያ ስልቶችን በመጠቀም፣ ባዕለጸጎች፣ ለቤተ ክርስቲያን በአደራ መልክ የሚሰጡትን የዐሥራት ብር እየወሰደ ኑፋቄውን ለማስፋፋት እያዋለው እንደሚገኝ ተደርሶበታል፡፡

ከኹለት ወራት በፊት፣ ለአኵስም ጽዮን ሙዝየም ማሠርያ ከአንድ ባዕለጸጋ የተለገሠውንና በአንዲት ሴት በኩል እንዲደርስ በቼክ የተሰጠን 6 ሚሊዮን ብር ከተቀበለ በኋላ የካደበት ኹኔታ በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡ በጎ አድራጊው ከሽያጭ ካገኙት ገቢ ያወጡትንና ለሙዝየሙ ማሠርያ እንዲደርስላቸው በአደራ የሰጡትን ዐሥራት፥ “እነርሱ ድንጋይ ሊጠርቡበት ነው፤ እኔ ወንጌል አስፋፋበታለኹ፤” በሚል ከሴቲቱ እንደተቀበለ ለመንበረ ፓትርያርኩ መረጃው በመድረሱ፣ ጉዳዩ በፖሊስ ተይዞ አሰግድም ጥያቄ እየተደረገለት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በማብራሪያው በቀረቡ ማስረጃዎችና በተካሔደው ውይይት፣ አሰግድ ሣህሉ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ የኑፋቄ እንቅስቃሴ እያራመደ እንደሚገኝና በወንጀል የሚስጠይቀውን ተግባርም መፈጸሙን ያመነበት ምልአተ ጉባኤው፣ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ ወስኗል፤ ይህንኑ ውሳኔ መሠረት ያደረጉ ትእዛዞችንም ሰጥቷል፡፡

በዚኽም መሠረት፡- 1) በቀረቡት የቪዲዮ ማስረጃዎችና ሰነዶች መሠረት፣ አሰግድ ሣህሉ ኑፋቄውን ላሠራጨባቸው ትምህርቶቹና ሥራዎቹ የሊቃውንት ጉባኤ ምላሽ እንዲያዘጋጅ፤ 2) ዐሥራት መሰብሰብን ጨምሮ በቤተ ክርስቲያን ስም የፈጸማቸው አድራጎቶች ኹሉ ተለይተው በሕግ እንዲጠየቅ፤ 3) የአሰግድ ሣህሉ አበሮች መኾናቸው የተገለጹት ከ37 ያላነሱ ማኅበራትና ግለሰቦች በዝርዝር እንዲታወቁና ከኑፋቄ ተባባሪነታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው እንዲገለጽላቸው ምልአተ ጉባኤው በውሳኔው አዟል፡

Advertisements

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s