በጀርመን የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በበርሊን ከተማ June 3 & 4 በቅርብ መነጽር ሲታይ

ዘንድሮ ይህ ፌስቲቫል ሲካሄድ በብዙ መልኩ ከቀድሞዎቹ ዝግጅቶች በተሳካ ነው ብሎ መጀመሩ የዚህን ጽሁፍ መጠነኛ የይዘት አቅጣጫ ይጠቁማል።77110-768x432

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በቅርብ መነጽር ያለበት ምክንያት ፌስቲቫሉ ከጀመረበት 1 ቀን በመቅደም ከፌስቲቫሉ ቦታ 50 ሜትር ባልራቀበት ሆቴል በማረፉና አካባቢያዊ ግንዛቤውም ቀድሞ በመጀመሩ ከዚያም እስከተጠናቀቀበትም ሰዓትና ደቂቃ በቅርብ ከማየቱም ባሻገር የዝግጅቱንም ሂደትና መልክ አብሮ በመቅረጹም በኩል ከኢትዮ ጀርመን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ሲመክርበት እንደነበረ ለመጠቆም ይወዳል።

ከዚህ በፊት የነበሩት ዝግጅቶች የ 1 ቀን ብቻ በመሆናቸው ከጉዞ ርዝመት ከነበሩት የአየር ንብረት ሁኔታ ጋር ተደማምረው ከነበረው ግዜ መጣበብ ጋር የነበሩብንን ጫናዎች ለማቅለል የሁለት ቀን ማድረጉን ተግባራዊ ለማድረግ ተመክሮበት ለዚህ ስኬታማ ውጤት በመደረሱ ሁሉም በዚህ ጉዳይ ቅድመ ሃላፊነት ተሰምቶት የመከረና ያስተባበረ የፌዴሬሽኑ አባሎች ምስጋና ሲያንሳችሁ ነው። መወያየትን መምከርን ግልጽነትን እውቀትን ከተላበስን ሁሉን ነገር በቅንነት ለመመርመር ይስችላልና በርቱ።
እንዲህ ነበር ያለፈው

ጁን 3 እና 4 ማለትም ቅዳሜና እሁድ በርሊን ከተማ ከመሃል ከተማው አንስቶ ገዙንድ ብሩነን የተባለውን የከተማውን ኣንድ ክልል ከወትሮው በተለየ የኢትዮጵያውያን መንደር ለማለት በሚያስችል መልኩ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተዋቡ ሴቶች እህቶቻችን ህጻናትና በኮፍያ ስከርቭና በዋልያዎቹ ደማቅ ማልያዎች የተዋቡ አባቶችና እናቶች ከነልጆቻቸው ወጣት ሴቶችና ወንዶች አቅጣጫቸውን ወደ ፌስቲቫሉ በማድረግ በከተማ የህዝብ ማመላለሻ ባቡርና በምድር ውስጥ የከተማ ባቡር እንዲሁም በግል መኪና በማሽከርከር በቅርብ ሆቴሎች የሰፈሩት ደግሞ በእግር መኳተን የጀመሩት ገና ከማለዳው 3 ሰዓት ሳይሆን ነበር።

ቅዳሜ በማለዳ ተፈጥሮም እለቱን በብርሃን ለማጀብ ከማንም ቀድማ ጸሃይዋን ልካ ነበርና የመጀመርያ አድራሻቸውን ፌስቲቫል ሜዳው ላይ ያደረጉትን የኢትዮ ሽቱትጋርት ስፖርተኞችን ማሞቅ በመጀመር ዓርብ ምሽቱን ዝግጅቱን ባጠናቀቀው ዲጄ አገራዊ የእረኛውን ክላሲካል ሙዚቃ ሲለቀው በሰማይ የሚበሩ ወፎችን እንደመፈለግም ቁልቁለት እንዲሚፈስም የወንዝነት ድምጽ እያስተጋባ ፍጹም ልዩ በሆነ መልኩ ወደ አገርቤት ልብን እየሰለበ የፌስቲቫሉም ጠረን ከቅርብ እንድናሸተው ማድረግ የጀመረው ገና ከጅምሩ ነው። ከግራና ቀኝም ቀድመው የመጡ ስፖርተኞችም በሙሉ ውበት ያለውን የተለያየ ማልያ ተላብሰው ሜዳ ውስጥ ውር ውር ሲሉ የፌስቲቫል አዘጋጆችም እዛው ያደሩ ይመስል በየስራ ድርሻቸው ተከፋፍለው ቅድመ ዝግጅታቸውን ጨርሰው በተያዘው ፕሮግራም መሰረት የስፖርትና ቴክኒክ ክፍሉ የቡድን ምዝገባ ሲጀምሩ ክለቦችም ኢትዮጵያ ሀገሬ የሚለውን የቴዲ አፍሮን ዘፈን እየጨፈሩበት ከአውቶቡሳቸው እየወረዱ ወደ ፌስቲቫሉ ግቢ ሲገቡ ማየት እጅግ ልብ ይማርክ ነበር።

ተሳታፊ ክለቦች በተወካዮቻቸው አማካይነት ምዝገባቸውን እንደጨረሱ በሁለት ምድብ በመከፈል በሁለቱ ሜዳ ላይ እንዲጫወቱ ድልድሉ አልቆ ዳኞችም ተመድበው ስፖርታዊው ውድድር በሰዓቱ ተጀምሯል።

ሁል ግዜ እንደሚደረገው አንድ ሁለት ጨዋታ ከተከናወነና ታዳሚዎ ችም በርከት ሲሉ ዝግጅቱ እንደሚከፈተው ሁሉ ወደ 13 ሰዓት ገደማ በስነ ስርዓት ተከፍቷል። የመክፈቻ ስነስርዓት በትናንሽ ባንዲራዎች አረንጓዴ ቢጫ ካኒቴራዎች ለብሰው ጣዕም ባለው ዜማ የበርሊን ህጻናት እማማ ኢትዮጵያ ሀገሬ እያሉ በመዘመር የመክፈቻ ስነስርዓቱን አድምቀውታል። ይህን ሲሰማ ስንቱ ሆዱ ባር ባር ብሎት ይሆን እጅግ ይመስጥ ነበር። ይህ በህጻናቱ እንዲሆን ያዘጋጀው የበርሊን እናቶችና ህጻናት ማህበር ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ህጻናቱንም በጥበብና በክብር እግዚአብሄር ያሳድግልን።

የክብር እንግዳ የዘንድሮውን ፌስቲቫል የዝግጅት ደረጃ ከፍ ካደረጉት ክንውኖች መካከል የክብር እንግድነት ደረጃው አንደኛው ነው ለማለት ግድ ይለኛል። አቶ ፍቅሩ ኪዳኔን የመጀመርያው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኛ የአፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽንና የአለም የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል የወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚደንቱ አማካሪን በእንግድነት ከፓሪስ እዚህ ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ ማስቻል ማለት ምን ያህል የኢትዮ በርሊን የስፖርት ማህበር ለስፖርታዊው ዝግጅት ትኩረት እንደሰጠው ለቀጣይ ታዳጊ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለሀገርና ለወገን የደከሙ ባለአደራዎችን ድካማቸውን እውቅና በመስጠት እንዲሁም ራእያቸውና ብልህ አመራራቸው ወደ ትውልዱ ሰርጾ እንዲገባ ለማስቻል በእንደዚህ አይነት ኢትዮጵያውያን በሚገኙበትና እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ደምቃ በስፋት በምትወደስበት ፌስቲቫል ላይ ማቅረብ የስፖርት ማህበሩን አመራሮችንም ክብርና ሃላፊነት ከፍ ያደርገዋል። በዚህ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል። በመቀጠልም አቶ ፍቅሩ በበዓሉ መክፈቻ ላይ እንዲሁም በዶቼ ቬሌ የራድዮ ቀጥታ ስርጭትና ከዝግጅቱም በኋላ ያስተላለፉት ጥልቅ ንግግርና ምክር እንድታዳምጡእጠቁማለሁ። http://www.dw.com/overlay/media/am

ዳኞች የኢትዮ በርሊን ስፖርት ማህበር ከፍተኛ አጽንዖት ከሰጣቸው ተግባሮች መካከል ስፖርታዊ ይዘቱ የፊፋን ህግ እንዲከተል በማለት የከተማውን 4 ፕሮፈሽናል ዳኞችና አንድ ኢትዮጵያዊ ዳኛ(አቶ ጥላሁን ጉደታን)በማቅረብ ተግባራቸውን በትክክል እንዲወጡ በማስቻል እግርኳሱም ለስፖርተኞችም ለተመልካችም እንዲጥም እንዲሆን አድርገዋል። በዚህ ልዩ ምስጋና እንዲቸራቸው ያሻል።

ክለቦች በእግርኳስ ጨዋታው በኩል ሁሉም ክለቦች በሚባል መልኩ በጣም በወጣቶች በመደራጀታቸው ያለው የጨዋታ ብስለት ፉክክር ቴክኒክ ልብ የሚማርክ ሲሆን ካለው ዝቅተኛ የሆነው የቱርኒር ሰዓት አመዳደብ የተነሳ የልባቸውንና የአቅማቸውን ያህል ሳይጫወቱ እያለቀባቸው ተሸናፊ ቡድኖች ላይ የሚያሳድረው ቁጭት ሃይለኛ ነበር።

አሰልጣኞች የአብዛኛው ክለብ አሰልጣኞች ቅድመ ኢትዮጵያ ላይ በእግርኳሱ ዘርፍ አሻራቸውን አሳርፈው የመጡ በመሆናቸውና እግር ኳስን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው በሜዳው አካባቢ የሚያሳዩት ተግባር ከዳኛ ጋር ያላቸው የንግግር ደረጃና ስነምግባር ከፌዴሬሽኑ አመራሮችና ከአዘጋጅ ቡድን ሃላፊዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት እጅግ የሚያኮራ ነበር። የቅዳሜ ወይም የጁን 3 ቀን ውሎ ሁሉም ክለቦች በየምድባቸው ያለውን የርስ በርስ ውድድር እንዲጨርሱ ማስቻል ነበርና በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት እንደታቀደው ሆኖ ከየምድባቸው ሁለት ሁለት ቡድኖች እንዲያልፉ ሆኗል። በዚህም ከምድብ 1 ኢትዮ ሽቱትጋርትና ኢትዮ ኮለን ከምድብ ሁለት ኢትዮ አዲስ ፍራንክፈርትና ኢትዮ ዘ በርሊን ኣልፈው ለእሁዱ ማጣርያ ራሳቸውን አዘጋጅተዋል።

ፌስቲቫሉ ቤሄም ሽትራሴ የተባለውን የከተማውን ረጅም ጎዳና ተደግፎ የተንጣለለው ባለ ሁለት እግርኳስ ሜዳ (በፊፋ ደረጃ) የፌስቲቫል ቦታ ሙሉ በሙሉ የታጠረ በመሆኑ መግቢያ በሩም አንድ ብቻ በመሆኑ ከፍ ብሎ በተሰቀለው ሰንደቅ አላማችንና የእንኳን ደህና መጣችሁ ጽሁፍ ስር ማለፉ እያንዳንዱን ታዳሚ ኢትዮጵያዊ ልባሱን ደርቦ ለመግባት ያስችል ነበር። በጸጥታ አስከባሪዎች በመስተናገድ በቀጥታ በግራና ቀኝ በተጣሉ ድንኳኖች ውስጥ ባህላዊ አልባሳት ኮፍያዎች ስከርቮች ቲሸርቶችን ለህጻናት የሚሆኑ ጌጣጌጦችን ወዘተ እየሸመቱ ወደ ዝነኛው የኢትዮጵያ የጀበና ቡና ድንኳን ያመራሉ።
በበርሊን የኢትዮጵያውያን የእናቶችና ህጻናት ማህበር ሙሉ በሙሉ የሚስተናገደው የቡና ድንኳን ሙሉ ቅዳሜና እሁድ ያለፋታ የቡና አቅርቦቱን ከቡና ቁርስና መዓዛ ካለው አገራዊ እጣን ጋር ያለ ድካም በፍቅር ሲያስተናግድ ስለነበር ለነበረው አገልግሎት በቦታው ለነበሩት እህቶችና እናቶች ምስጋና ይገባቸዋል።

የፌስቲቫሉ አስተዋዋቂና ዲጄ ሙሉ በሙሉ የተዋጣለት የመድረክ አስተዋጽኦ እንዲሆን በማሰብ የተሳካለት የማስተዋወቅ አገልግሎት ከዲጄ ጋር እንዲሆን በማሰብ የኢትዮ በርሊን ስፖርት ማህበር እውቁን አስተዋዋቂና ፌስቲቫል አጋጋይ አቶ ዘለአለምን ከታዋቂ ዲጄ ጋር በመመደቡ እጅግ የሚበረታታና የተሳካ አገልግሎት እንዲሆን አስችሏል። ያለምንም እክል የሙዚቃም ሆነ የግንኙነት መስመር ለደቂቃ ሳይቋረጥ የተዋጣለት በሚባል መልኩ አገልግለዋል።በዚህም የህዝቡን ልብ ትርታ እየተካከተሉ ያጫውቱ የነበረው ወቅታዊ ሙዚቃዎችና እራሳቸውም ከመድረክ ላይ ሆነው በሚያሳዩት ባህላዊ ዳንኪራዎች የፌስቲቫሉ ድምቀቶች ነበሩ። በዚህም ኮርተንባቸዋል።

ምግብና መጠጥ የታዳሚውን ህብረተሰብ በርክቶ መምጣት ግንዛቤ በመውሰድ በርካታ የምግብ መደብሮች በመኖራቸው መጉላላት የሚባል ነገር ሲጀምር የሚታሰብ አልነበረም። ሲቀጥል ደግሞ ሰሃን የሚደፋው የምግብ ብዛት በስስትና በንግድ ላይ ያላማተረ ህዝባዊ አግልግሎት እንደነበረ የሚያሳይ ለልጆችም የሚሆን ከህጻናት ምግብ እስከ አይስክሬም ለስጋ ወዳጅ ወገኖቻችን ደግሞ በግሪል ወይም በፍም የጋለ ስጋ በሃምበርገር መልኩ ሲያስተናግዱ ከርመዋል።

የመጠጥ አገልግሎቱም የለስላሳ መጠጥና ቀዝቃዛው የጀርመን ቢራ ያለ ማቋረጥና ያለ ወረፋ በቂ ሰራተኞች በመመደባቸው እክል ያልገጠመው አገልግሎት ተካሂዷል።
የመጀመርያ ህክምና እርዳታ የእርዳታ ሰጪዎች በሁለቱም ሜዳዎች ላይ በመገኘት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተጫዋቾች ሲረዱ ተስተውሏል።

ስነስርዓት ሲጀምር እስከዛሬ በየፌስቲቫሉ ሲታዩና እንደ አንድ አስቸጋሪ ነውርና ተግባር የነበሩት የጫትና የሺሻ ስርጭቶች ወይም አገልግሎቶች አንድም አልነበሩም። ይህም ትልቅ የትውልድን መሻሻል ለቀጣይ ህጻናት የማሰብን ባለአደራነት ያሳያል። ይህ ደግሞ ከየትም የመጣ አይደለም፡፡ ከኛው ከህብረተሰባችን የመጣ ብርታት እንጂ። የቡድኖችን የተጨዋቾች ተዋጽኦ ሲታይ ያ የእከሌ ልጅ ነው ይህ የእከሌ ልጅ ነው መባሉ ራሱ ክለቦችን ቤተሰባዊ ቅርርብ የማድረግን ወላጆችም ለእንደዚህ አይነት ስብስቦች ግዜና ትኩረት የመስጠት በዛው ደግሞ ተወራርሶ የሚሄደው ደግሞ ጨዋነት ክብር ማንነት በመሆኑ እነዚህ ደግሞ የአስነዋሪ እጽ ማራቂያና ስፖርቱ ደግሞ ወላጆችንና ልጆቻቸውን ከወገኖቻቸው ማቀራረብያ በመሆኑ ሁሉም ከተባበረ አስነዋሪ ነገሮችን አብሮ ማገድ ስለሚቻል ዘንድሮ አንድ የጫት ዘለላ ያልታየበት አንድም የሺሻ መቃ ያልታየበት እንዲሁ ብቻ ፌስቲቫል ፌስቲቫል ሲጫጫስበት የነበረ በመሆኑ የተሟላ ስነ ስርዓት ነበር በሚያስችል መልኩ ተፈጽሟል።

የእሁድ ውሎ ጁን 4

የቅዳሜው ዝግጅት ሲቆለፍ የእሁዱን አጀማመር አስምሮበት ነበርና ያደረው ከማለዳ ጀምሮ ሊኖር የሚችለውን ቅድመ አየር ንብረት ማለትም ከማለዳው ጀምሮ እንደሚያካፋ ወፏ አሳብቃ ስለነበር ከዚያም ባላፈ የበርሊን ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያንም ታቦት የሚነግስበት እለት በመሆኑ ሁለቱን ዝግጅቶች በማናበብ ከቀኑ 13 ሰዓት ጀምሮ እንዲቀጥል ተደርጎ በመታደሩ ስፖርታዊ ውድድሩም ከ 14 ሰዓት እንደሚጀምር በመነገሩ ዝናቡም በቀጠሮው መሰረት እሁድ ከጠዋት ጀምሮ እየረገጠ ወደ ከሰዓት በኋላው ግን ደመናውም እየተገለጠ ዝናቡም እየለቀቀ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ መሰረት ደቂቃ ሳይዛባ ውድድሮቹም ፌስቲቫሉም በየሰዓታቸው ተጀምረዋል።

የበርሊን ቅዱስ ዓማኑኤል ቤተ ክርስትያን ድርሻ የዚህ ፌስቲቫል ልዩ መሆንና ውበት በተለይ በጀርመንና አካባቢው ለሚኖሩ ህዝበ ክርስትያን በማሰብ የኢትዮ በርሊን ስፖርት ማህበርና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የበርሊን የቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያን አባት ካህንና የሰበካ ጉባኤ አባሎች በመቀናጀት በመተባበር ሰዓቶቻቸውን በማቀራረብ ያደረጉትን ትብብር ሳናደንቅ አናልፍም። ቤትክርስትያኗም ምዕመኗን በቤትክርስትያን ዝግጅታቸውና በፌስቲቫሉ ቦታ ላይ በማሰማራት ያደረግችውን የተሳካና የተዋጣለት እርዳታ ብዙዎች ሲያመሰግኗት ከፌስቲቫል ቦታው መስማት እጅግ ያረካ ነበር። ስፖርታዊው ውድድር የጀመረው በኢትዮ ሽቱትጋርትና ኢትዮ ዘበርሊን መካከል ሲሆን በድምሩ 40 ደቂቃ ተጫውተው ባዶ ለባዶ ተለያይተው በፍጹም ቅጣትምት ኢትዮ ሽቱትጋርት አሸንፏል።

የህሊና ጸሎት የቀድሞ ኢትዮጵያ ቢሄራው እግርኳስ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና የእግርኳስ ቡድን ተጫዋች የአሰግድ ተስፋዬን ሞት በማስመልከት በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ መካከል ሙሉ ሜዳው በጸጥታ በመሆን የ 1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

የህጻናት እግርኳስ ለህጻናት በተያዘው ፕሮግራም መሰረት የኢትዮ በርሊን ህጻናት ቡድን ከመላው ጀርመን ቤተሰቦቻቸውን ተከትለው ከመጡ ህጻናት ጋር እንዲጫወቱ ተደርጎ በጣም ማራኪ የሆነ የልጆች ጨዋታ ተካሂዶ የበርሊን ህጻናት አሸናፊ ሁነዋል።
በመቀጠል በኢትዮ አዲስ ፍራንክፈርትና በኢትዮ ኮሎኝ መከካል በተደረገው ከ 40 ደቂቃ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች አቻ

በመውጣታቸው በፍጹም ቅጣት ምት እንዲለያዩ ተደርጎ የፍራንክፈርት ቡድን አሸናፊ ሁኗል።
በዚህም መሰረት የመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮ ሽቱትጋርና ኢትዮ አዲስ ፍራንክፈርት መካከል እንደሚሆን ተረጋግጦ እስከዚያው የዲጄ ስራ ድምቀቱን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የባህላዊው ዝግጅት በስፋት ቀጥሏል።

በዚህ መልኩ ፌስቲቫሉ ወደመጠናቀቁ እያመራ በአንጻሩ ደግሞ ተፈጥሮም ገደብ የለሽ ብርሃኗንና ሙቀቷን እየለገሰች ህዝቡን ስሜቱን መገደብ ባልቻለ መልኩ ወደ መድረኩ በመጠጋት አንዴ የጎንደርኛውን የጎጃሙን የሸዌውን ኦሮሚኛውን ትግርኛውን ጉራግኛውን ወላይታኛውን ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው ሙዚቃ ከመድረክ እየተንቆረቀረ ስፖርተኞችና ህዝቡ የጥንት ጀግኖችን ስራ የሚወያድሱትን የነአጼ ቴዎድሮስን ስም እያነሱ በመጨፈር እልልታውና ፉከራው እስክስታው ገደብ አልነበረውም። በተለይ ውድድራቸውን በቅዳሜው ቀን የጨረሱት ስፖርተኞች ሙሉ ግዜያቸውን ከዲጄው ጋር እየጨፈሩ የመጡበትን ሂሳብ በበቂ ሁኔታ አወራርደዋል።
የፍጻሜው ጨዋታ በጊዜው ሰሌዳ መሰረት የፍጻሜው ጨዋታ ቡድኖችን በመምራት የመሃል ዳኛው አቶ ጥላሁንና ሁለቱ የመስመር ዳኞች ቦታቸውን እንደያዙ የክብር እንግዳውን አቶ ፍቅሩ ኪዳኔን በመያዝ የኢትዮ በርሊን ቡድን መሪ አቶ በላይነህ ተሾመ ወደ ሜዳ በመግባት ከሁሉም አስተዋውቀው መልካም ውጤት ተመኝተዋል።
በጣም ከፍተኛ ፉክክርና ቴክኒክ የተመላበት ጨዋታ ተካሂዶ የኢትዮ አዲስ ቡድን አሸናፊ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል። የሽልማት ስነ ስርዓት
የኢትዮ በርሊን ስፖርት ማህበር እንደ ሌሎቹ እቅዶች ከፍተኛ አጽንዖት ከሰጣቸው ክንውኖቹ ውስጥ ሽልማቶቹ ናቸው። በመሆኑም ከዳኞች ጀምሮ እስከ ተሳታፊ ቡድኖች ሁሉም የምስክር ወረቀትና በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንድራ የተዋበ ሜዳልያ እንዲሁም የተለያዩ ዋንጫዎች ተዘጋጅተው ተበርክቷል።
ሽልማት ያበረከቱትም
አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የክብር እንግዳ ለአሸናፊዎች ዋንጫና ሜዳልያ

አቶ ዘላለም(የጌድዮን አባት) ለኮከብ ጎል አግቢና ኮከብ ተጫዋች
ወይም ብዙዎች በሚያውቁት በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ለአርሰናል የሚጫወተውና ለአሜሪካ ቢሄራዊ ቡድን ምርጥ ተጫዋች የጌድዮን አባትን በሽልማት ስነስርዓት ለብዙዎች አርዓያነት እንዲኖረው በማለት የማበረታቻ ሽልማት እንዲሰጥ መጋበዙ በብዙ መልኩ ይህን ፌስቲቫል በጥናትና በእወቀት መደገፉን ያሳያል።

አቶ ካሱ ለገሰ ከኢትዮ ጀርመን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ለዳኞች ምስክር ወረቀትና ሜዳልያ እንዲሁም ለኢትዮ በርሊን ስፖርት ማህበር የመልካም ዝግጅት ሽልማት ለማህበሩ ሊቀመንበር ለአቶ ታደሰ ልዩ ሽልማት

አቶ በላይነህ ተሾመ ከኢትዮ በርሊን ለተሳታፊ ክለቦች ለሁሉም ከምስጋና ጋር የተሳትፎ ምስክር ወረቀት እንዲሁም ለሶስቱም ሸላሚዎች የበርሊን 2017 ዝግጅት ማስታወሽያ ልዩ ሜዳልያ ፌስቲቫሉን በድምቀት ለመሩት የመድረኩ ሰዎች ለአቶ ዘላለምና ለዲጄ ልዩ ሜዳልያ

በዚህም መሰረት እንደየደረጃቸና ተሳትፏቸው ከእንግዶቹ ሽልማት የተበረከተውን ለመዘርዘር ያህል

የህጻናት አሸናፊ
የህጻናት ሁለተኛ
የጸባይ ዋንጫ
ኮከብ ጎል አግቢ
ኮከብ ተጫዋች
የሁለተኛ ደረጃ አዋቂዎች
አንደኛ አሸናፊ አዋቂዎች

 

ኢትዮ በርሊን
ኢትዮ ጀርመን
ኢትዮ ሀምቡርግ
ከኢትዮ ዘበርሊን 9 ቁጥር ኤፍሬም

ከኢትዮ ሽቱትጋርት 9 ቁጥር ሉታስ ኢትዮ ሽቱትጋርት

ኢትዮ አዲስ ፍራንክፈርት

በዚህ መሰረት ፌስቲቫል ሜዳው ላይ የነበረው የመድረክ ስነርዓት አልቆ ለቀጣይ 2 ሰዓታት ያህል ሳይቋረጥ የባህል ፕሮግራሙ ሜዳው ላይ ቀጥሎ ግዜው ለአይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ፕሮግራሙ እየተጠናቀቀ ማስታወቅያም ወደ ቀጣይ የሌሊት የመዝግያ ፕሮግራም ወደ ጸሃዬ ዮሃንስ ማምራቱን ተያያዘው።

ሰዓቱን ጠብቆ ይህ ፕሮግራም እንደተጠናቀቀ ስፖርተኞችም አንድ ሳይቀሩ ወደ ምሽት ፕሮግራሙ በመሄድ ዘና ፈታ ሲሉ አድረዋል። የኢትዮ በርሊን ስፖርት ለስፖርተኞች ቀድሞ በገባው ቃል መሰረትም ከመግቢያው ዋጋ ላይ የ 5 ኦይሮ ቅናሹን ተግባራዊ አድርጓል። ጥሩ ማባረታቻና ስፖርተኞችን መደጎምያ በመሆኑ እንዲህ አይነት አርአያነት ሊበረታታ ይገባል።

ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነገር ዓመታዊው የበርሊን ከተማ ኢንተናሽናል የባህል ፌስቲቫል ላይ በተለይ ቅዳሜን ሌሊት እንዲሁም ሰኞ እለትን አብዛኛዎቹ እንግዶች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙ ይህን ሁሉ ከአጽናፍ አጽናፍ ያሉ ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ፌስቲቫሉ በነዚህ ቀናት እንዲሆን በጀርመንም ሰኞን የበዓል ቀን መሆኑን ከግምት ውስጥ አስታካሃችሁ ፕሮግራም ለነደፋችሁ ላስተባበራቸሁ ለመራችሁ ሁሉ ምስጋናውን ይህ ጽሁፍ ብቻ አይገልጸውም።

በዝግጅታችሁም እጅግ እንደረካችሁ ለማወቅ ምስክር ማቆም የሚያስፈልግም አይመስለኝም ይልቁንም ማነው ባለ ተራ የሚል ያሬዳዊውን ዜማ ወደ ክለቦቹ ለቃችሁ እርፍ እንዳላችሁ ልቤ ይሰብቀኛል።

ካሱ ለገሰ ከጀርመን ኑርንበርግ

kassule30@yahoo.de

Advertisements

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s